በመከራ ቀን እንዴት መቆም ይቻላል?

armor-of-god

– ዳዊት ወርቁ

አነሰም በዛ መከራ በአማኝ ህይወት መከሰቱ እውነት ነው:: የመከራው አይነት ይለያይ ይሆናል እንጂ መከራ አለ:: የክርስትና ጎዳና መከራ አልባ ነው ማለት ፈጽሞ አይቻልም::

መከራዎች ልዩ ልዩ ናቸው:: አንዳንዱ በበሽታ አንዳንዱ እጅግ ከባድ በሆነ ድህነት (ኢኮኖሚ ልሽቀት) ውስጥ ያልፋል:: አንዳንዱ ተምሮ አቅም እያለው መሥራት እየቻለ በሥራ ማጣት ይሰቃያል:: ሌላውም የራሱ የሆነ የሚያልፍበት መከራ አለው:: መከራ በሰዎች ላይ ባንድም በሌላም ይመጣል::

መከራን በራስ ኅይል  ማስቆም አይቻልም:: በመከራ ውስጥ ስናልፍ ግን  መከራን የምንቋቋምበት ጸጋ እንደምናገኝ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጽፏል::

“አሁንም ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥ እስራኤልም ሆይ፥ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ፥ አንተ የእኔ ነህ።
በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም፤ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፥ ነበልባሉም አይፈጅህም።” (ኢሳያስ 43:1)

መከራ ችግር ስቃይ በህይወት አጋጣሚ የሚከሰት ሃቅ ነው:: ማንም እንደሚያልፍ በእሳት ውስጥ እናልፋለን:: ማንም እንደሚያልፍ በውሃ ውስጥ እናልፋለን:: ነገር ግን ማንም በእሳት ውስጥ አልፎ እንደሚበላው አንበላም:: ምክንያቱም እሳቱ ውስጥ እግዚአብሔር አብሮን አለና:: ማንም በወንዝ ውስጥ አልፎ እንደሚሰምጥ አንሰምጥም:: ምክንያቱም የወንዙ ባለቤት አብሮን አለና::

በየትኛውም መከራ ውስጥ ስናልፍ ከመከራው በላይ የሆነው ጌታ አብሮን ካለ መከራው አይጎዳንም:: እግዚአብሔር ከኛጋ ስላለ በመከራው ውስጥ እናልፋለን እንጂ አንበላም::

አንድ ጊዜ የጌታ ደቀ መዛሙርት ታንኳቸው በወጀብ ስትናጥ በጣም ፈሩ:: ጮሁ:: አለቀልን አሉ:: የወጀቡ ባለቤት ግን አብሯቸው ነበረ:: ለዚያውም በአካል:: ተኝቶ ነበር እርሱ እንዲያውም:: እየተጯጯሁ ቀሰቀሱት:: በመከራ ላይ ነበሩ:: እሱ ግን ማዕበሉንና ነፋሱ ገስጾ ጸጥ አሰኘው::

ዛሬ በምን አይነት ማዕበል ውስጥ እያለፍሽ/ክ ነው? . . . የወጀቡ ፈጣሪ አብሮህ ነው:: ታንኳህን ሊያናውጥ የመጣው አውሎ ጸጥ ይላል:: አንተ ብቻ እርሱ አብሮህ እንዳለ እርግጠኛ ሁን::

ሌላው በመከራ ቀን መቆም የሚቻለው የእግዚአብሔርን የጦር መሣሪያ በመታጠቅ ነው:: ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በክፉው ቀን ለመቆም እንድትችሉ የ እግዚአብሔር የጦር ዕቃ ሁሉ አንሱ ሲል ይመክራል::

ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ። (ኤፌሶን 6:10 )

ለመሆኑ የእግዚአብሔር የጦር መሣሪያ ምንድነው?

(ይቀጥላል . . .)

This entry was posted in AK 3:16, የክርስቲያን ማስታወሻ- Christian Diary, Gospel - ወንጌል, Hope - ተስፋ. Bookmark the permalink.

Leave a comment