ቆንጆ-ሰነፍ ሚስቴ

(በተለይም አግብተው ግራ ለተጋቡ ባሎችና ክርስቶስ የሞተላትን ቤተክርስቲያን ለሚሳደቡ የተጣፈ ተረክ)

 

(C) ዳዊት ወርቁ

leniwaniedziela8ተንደረደርኩና ውብ ሚስት አገባሁ:: ምንም ሰሃ የማይወጣላት:: ግና እንዳለመታደል ሆኖ ሚስቴ በቤት ውስጥ ብዙ ነገር ይጎላታል:: ለምሳሌ ከሙያ ሙያ የላትም:: ሽሮና ዶሮ አንድ ላይ ቀላቅላ የምትሠራ ፍጡር ናት:: አልጋ ላይ ተመቻችታ ከተጋደመች ጎትቼ ነው የማወርዳት:: የተበላበት ዕቃ ሳይታጠብ በመቆየቱ ሌላ መጥፎ ጠረን እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል:: የቤቱ ሥርዓት በአጠቃላይ ትርምስምስ ብሏል:: ይባስ ብሎ ነዝናዛና በትንሽ ትልቁ ውሃ ቀጠነ ናት:: እናም መረረኝ:: ብዙ ጊዜ ልመክራት ጥሬያለሁ:: ግን ያው ናት:: ውሃ ቢወቅጡት እምቦጭ ሆነችብኝ:: እንዳልፈታት የቃል ኪዳን ሚስቴ ናት:: በዚያ ላይ እንደ ዝሙት አይነት ነገር ሚስት የሚያስፈታ ኃጢያት የለባትም:: ላም እሳት ወለደች ሆኖብኝ . . . አስቤ አውጥቼና አውርጄ ወደ ቤተክርስቲያኔ መሪ ሄድኩኝ:: . . .

“ምን ትመክረኛለህ? . . .” ጠየኩት:: መሪው በረጅሙ ከሳቀብኝ በኋላ “ገልቱ፣ ሰነፍ፣ ነዝናዛና፣ ደንቆሮ ሚስት አግብተህ ምን በወጣህ ትሰቃያለህ ፍታትና እረፍ!” አለኝ::

“ፓስተር ሚስቴኮ በላዬ ላይ ዝሙት አልሰራችም እንዴት እፈታታለሁ?” አልኩት:: ፓስተሬ “ቢዚ ነኝ ሌላ ጊዜ አናግረኝ” ብሎ ጥሎኝ ነካው::

 

በጣም አዝኜ ወደ ቤቴ እየተመለስኩ እያለ . . . አንድ ጓደኛዬን አገኘሁት:: ችግሬንም አካፈልኩት:: በጥሞና ከሰማኝ በኋላ . . . “እስቲ እንዲህ አርግ” አለኝ . . . “የሚስትህን ሥራ አንተ ሥራው”::

“ምን?”

“ይገባኛል አንተም የራስህ የሥራ ድርሻ አለ:: ነገር ግን እስቲ ዋጋ ከፍለህ የሷንም ደርበህ ሥራው:: ከዚያ ለውጡን ትታዘባለህ::”

እንዳለኝ የቆንጆዋ ሚስቴን የሥራ ድርሻ ተረከብኩ:: የሥራ ሰዓቴ ከመድረሱ በፊት ቀደም ብዬ ተነስቼ ቁርስ እሠራራና ከእንቅልፏ ቀስቅሼ አበላታለሁ:: እንዲያውም የሆነ ቀን ደሞ የምግብ አሠራር የሚያስተምር መጽሐፍ ገዝቼ እኔ ነኝ ያለ የዶሮ አሩስቶ አስኮመኮምኳት:: ከስራ ቶሎ ተመልሼም የቆሸሹ ዕቃዎችን አጥቤ ልብሶቻችንን ላውንደሪ አርጌ የተዘበራረቁ ዕቃዎችን አስተካክዬ እጨርሳለሁ:: ቆንጆዋ ሚስቴ በዚህን ሰዓት ሁሉ አልጋ ላይ ናት:: ጣፋጭ እንቅልፍ ላይ::

ነገርዬውን ለብዙ ቀናት ቀጠልኩ:: የውነት ለመናገር ያሰለቻል:: ግን ሚስቴን እወዳታለሁ:: እሷን ከማጣ ጣፋጭ ምግብ ጥንቅር ብሎ ይቅርብኝ:: እሷን ከማጣ ቤቱ አይደለም መቆሸሽ ለምን ቆሼ ሠፈር አይሆንም። አይደለም ተኝታ መዋል ለምን ሣር አይበቅልባትም።

 

በንዲህ ያለ ሁናቴ ቀናት ሄደው ወራት ተተኩ:: ዓመታትም አለፉ:: አሁን እኔ ሚስት እሷ ባል ሆናለች::

 

,

 

,

 

,

 

የሆነ ቀን ለማኝ ሳይጠዳዳ ቤታችን ውስጥ ጉድጉድ የሚል ድምጽ ሰማሁ:: አይኔን ብገልጥ ቆንጆዋ ሚስቴ ካጠገቤ የለችም::

“ቆንጆዋ ሚስቴ ቆንጆዋ ሚስቴ” ተጣራሁ::

“አቤት ትጉሁ ባሌ”

“ወዴት ሄድሽ? ምን እየሠራሽ ነው?”

“አለሁ ቁርስ እየሰራሁ ነው”

“ምን? እኔ የት ሄጄ? ኧረ ነይ ተኚ እኔ አለሁኮ . . .”

አሻፈረኝ አለች:: ጣት የሚያስቆረጥም ቁርስ አበላችኝ:: ወይ ግሩም ሚስቴን ምን አገኛት?!

የሌት ልብሴን ቀይሬ የሥራ ልብሴን ልለብስ ስሰናዳ የተተኮሰ ሸሚዝና ቦላሌ ተወልውሎ ከሚያንጸባርቅ ጫማጋ ተቀምጦ አገኘሁ::

“ቆንጆዋ ሚስቴ”

“አቤት ትጉህ ባሌ”

“ይሄንንም አንቺ ነሽ እንዲህ ያረግሽው?”

“ኧረ አይደለሁም”

“ታዲያ ማነው?”

“ትጉሁ ባሌ ነዋ::”

“አልገባኝም??”

“ሲቆይ ይገባሃል:: በል አሁን ወደ ሥራህ በሰላም ሂድ” ብላ ላፍታ ምድርና ሰማዩን ያዞረብኝ እንደ ማር የጣፈጠ አሳሳም ስማኝ ወደ ማጀት ዘለቀች::

 

ከሥራ ስመለስ ቤቱ ከጥዳቱ የተነሳ የኔ ቤት እስከማይመስለኝ ሆኖ ጠበቀኝ:: ቆንጆዋንም ሚስቴን አልጋ ላይ ሳይሆን ሥራዋን ሁሉ ከውና አጊጣና ተውባ ምሳ ስታሰናዳ ነበር ያገኘኋት::

“እኔ ምልሽ ውቧ ሚስቴ ይሄ ሁሉ ለውጥ እንዴት ነው?” አልገባኝም:: ጠየኳት ከናፍሮቿን ከከናፍሮቼ እያጎዳኘሁ::

“ኬትም አልተማርኩትም አንተው ነህ ያጋባህብኝ:: እንደባል ትዛዝ ሳይሆን ፍቅር ነው ያስተማርከኝ:: እኔም ካንተ ያየሁትን ነው ያደረኩት:: አዲስ ነገር የለም:: ሚስትህን ትሠራታለህ እንጂ አታሠራትም::”

ዓይኖቼ የደስታ እምባ አቆሩ:: የኃይማኖት መሪዬ ሳይሆን ወዳጄ የመከረኝ ምክር ሠርቷል::

ወይ ጉድ ለካ ለሚስቴ እየሠራሁላት አልነበረም እየሠራሁዋት እንጂ?

 

(ራስ ዳ. እንደጣፈው)

ጁላይ 8/2017

እስሊበር እስፕሪንግ፣ ሀገረ ማርያም

Advertisements
Posted in AK 3:16, የክርስቲያን ማስታወሻ- Christian Diary, ጊዜው - The Time, Backlog - ማህደረ ጉዞ, Church - ቤተክርስቲያን, Essay-ወግ, Gospel - ወንጌል, Identity - ስብዕና, Jesus - ኢየሱስ, Life - ሕይወት, Love - ፍቅር, Marriage - ትዳር, People-ሰዎች | Leave a comment

ሴት ስትገለጥ

(በተለይ ላላገቡ ወንዶች የተፃፈ)
(C) ዳዊት ወርቁ
እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት።
(ኦሪት ዘፍጥረት 2: 18)
1. ሴት ሴት ሲሸት
love-cartoon-pic-getty-images-85892412በዔደን ገነት ውስጥ አዳም ብቻውን ባይሆንም ብቸኛ ነበር:: ምን የእግዚአብሔር ኅልውና አብሮት ቢሆን ደግሞም በሰማይ ወፎችና በምድር እንሥሳት ቢከበብ አዳም ብቸኛ ነበር:: ዙሪያ ገባው ወና ነው። ሰው ሰው አይሸትም። ሴት ሴት አይሸትም። ወደ ቀኝ ዞር ሲል ስማቸውን እንኳ የማያውቃቸው እንስሶች ናቸው:: ወደ ላይ ቀና ቢል ወፎችና አሞሮች ናቸው:: ወደታች ዝቅ ቢል ተሳቢ እንስሳት ናቸው:: ወደ ግራ ቢዞር ዙሪያ ገባው አበባና ደን ብቻ ነው:: ብቸኝነቱ ልክ እሱን የምትመስል ተቃራኒ ፍጡር ስለሌለች ነው:: ሴት ስለሌለች ነው። ቢጤው ስለሌለች ነው:: ሌሎቹ እንስሳት ግን ተባዕት ከእንስት ናቸው:: ከአዳም በቀር ሁሉም ከቢጤው ነው:: አዳም ብቻውን ባይሆንም ብቸኛ ነበር:: ብቸኝነቱን ሲያስብ ምናልባት ይቆዝም ይሆናል:: ምናልባት ጸሐይ ስትወጣና ስትጠልቅ በሀሳብ ይፈዝ ይሆናል:: ተባእቱ ተ እንስቱ መላ እንስሳቱ ፍቅር ሲሠሩ ስለ ራሱ እያሰበ ግራ ይጋባ ይሆናል። ነገር ግን አዳም ብቸኝነቱን የምትጋራው ቢጤው ከጎኑ እንደነበረች በፍጹም አላወቀም:: የምታስፈልገው ሴት ሩቅ አልነበረችም። ከጎኑ ነበረች። በከባድ እንቅልፍ እስታልወደቀ ድረስ ግን አልተገለጠችም።
አንዳንዴ ብቻ ሳይሆን ሁልግዜ ህይወት እንዲያ ናት:: ያላገባንና በብዙ ሴቶች ተከበን ግራ የገባን ወንዶች ምን በሴቶች ጭን እየተደበቅን ብቸኝነትን ለማባረር ብንጥር እስታሁን ብቸኞች ነን:: ምክንያት? . . . ከከበቡን እንስት መሀል ቢጤያችን የለችማ! ስለዚህ ልክ እንደ አዳም ሴት ሴት ሊሸተን ይችላል። ሴት ምን ምን ትሸታለች? ተብሎ ቢጠየቅ ብቸኝነት ያንጠራወዘው አዳም ቀድሞ እጁን ያወጣል። ስለዚህ አንዳንድ ሰዎች በተለይም የትዳር ጓደኛ መፈለግ ያታከታቸው የኔ ሚስት ገና አልተፈጠረችም ይላሉ:: ይሄ የስንፍና ወይም ያላዋቂነት ንግግር ይመስለኛል:: ሔዋንህማ ከጎንህ ናት። ችግሩ አለመገለጧ ነው። ለምን አልተገለጠችም?. . . ምናልባት ብቸኝነትህ መልካም ይሆናል። ወይም ደግሞ ብቸኝነትህ መልካም አይደለም እስኪባል ድረስ መቆየት ይኖርብህ ይሆናል።
እግዚአብሔር በርግጥም ለአዳም ሄዋኑን መግለጥ ያለበት ሰዓት ሲደርስ ገልጦለታል:: ሔዋን ከመገለጧ በፊት ግን አዳም በከባድ እንቅልፍ እንዲወድቅ ተደርጓል:: ከዚያ በኋላ ነው ውስጡ የነበረችው ሴት የወጣችው:: ሔዋን በአዳም መሻት መሰረት የተፈጠረች ሳይሆን የተገለጠች ናት:: በነገራችን ላይ በመፍጠር ሂደት ሴት ከወንድ ቀጥሎ ሳይሆን ዕኩል ነው የተፈጠረችው::
( እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ዘፍ 1: 27)
በመግለጥ ሂደት ነው ቀጥሎ የምትሆነው:: ስለዚህ እንደ አዳም ስጋ ለብሳ በገነት ውስጥ ባትንቀሳቀስም ሴት ተፈጥራ ነበር:: በርግጥም ሔዋን በአዳም ውስጥ ሆና ትንቀሳቀስ ነበር:: ራሷን ችላ ስጋ ለብሳ የምትንቀሳቀስበት ጊዜ ግን ገና ነበር:: የመገለጥ ጊዜዋ ስላልደረሰ እግዚአብሔር አልገለጣትም:: ወይም ደግሞ መገለጧ እንደ አዳም ስሜትና ፍላጎት ይሆናል:: ምናልባት አዳም ብቸኝነቱ መልካም ቢሆንስ ኖሮ? . . . ሴት ላትገለጥ ትችል ነበር ማለት ነው? . . . አይመስለኝም:: ምክንያቱም የእግዚአብሔር ዓላማ በራሱ መልክ የፈጠረው ሰው በምድር ላይ እንዲበዛለትና ምድርን እንዲሸፍንለት ወይም እንዲሞላለት ከሆነ ሴት የግድ መገለጥ አለባት። በነገራችን ላይ እግዚአብሔር አዳምንና ሔዋንን ብዙ ተባዙ ብሎ የባረካቸው አስቀድሞ ሴት ሳትገለጥ ነው።
(እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው። ዘፍ1: 28)
ሰው መንፈስ ስለሆነ ለመባዛት ስጋ ያስፈልገዋል:: አንድ ጊዜ እግዚአብሔር ዘሩን በአዳም ውስጥ አድርጓልና:: ከዚያ በኋላ ስጋ ነው የሚቀረው:: ስጋ ደሞ ዋነኛ ጥቅሙ በቁሳዊው ዓለም ለመኖርና ብዙዎችን ለማብዛት ነው:: መንፈስ የሆነው ሰው ግን ዘሩ አንድ ነው:: ያም ዘር እግዚአብሔርን ይመስላል:: የማይባዛ የማይከለስ ዘር ነው:: መንፈስ ነውና:: በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረው መንፈስ የሆነው ሰው በቁሳዊው ምድር ላይ የሚኖርበት መኖሪያ (ስጋ) ገና አልተበጀለትም ነበር:: መንፈስ የሆነው ሰው ጾታው ሁለት ነው:: ወንድና ሴት:: በስጋ ውስጥ እስኪገባ ድረስ በአንድ ስም ሰው ተብሎ ይጠራም ነበር:: ሰው ማለት ደሞ ወንድና ሴት ማለት ነው:: ሰው = ወንድ + ሴት:: በዘፍጥረት ምዕራፍ 2 ላይ ግን ሰው ለሁለት ጾታ ይከፈላል:: ከዚያ በፊት ግን ይህ ስጋ የለበሰው መንፈስ የሆነ ሰው ረዳት እንደሚያስፈልገው እግዚአብሔር ተረዳ::
(እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት። ዘፍ 2: 18)
2. የማትረዳ ረዳት
እዚህጋ ነው የሚገርመኝ:: እግዚአብሔር ረዳት እንፍጠርለት ብሎ ለአዳም ያመጣለት ረዳት እንስሶችን ነው:: እንጂ ከአዳምጋ አብሮ የፈጠራትን ሴት አይደለም:: በርግጥ እግዚአብሔር እንስሶቹን ወደ አዳም ሲያመጣ አዳም እንደርሱ ያለ ረዳት በሚፈልግበት ሁናቴ እግረ መንገዱንም ለስም አልባዎቹ እንስሳት ስም እንዲያወጣላቸው ነው::
(እግዚአብሔር አምላክም የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉ ከመሬት አደረገ፤ በምን ስም እንደሚጠራቸውም ያይ ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው፤ አዳምም ሕያው ነፍስ ላለው ሁሉ በስሙ እንደ ጠራው ስሙ ያው ሆነ። ዘፍ 2:19)
አዳም ረዳቱ እንድትሆን ማንን አስቀድሞ እንደመረጠ ባላውቅም ነገር ግን እንገምት:: ለምሳሌ ላምን መረጠ እንበል በቀንዷ እየወጋች አስቸገረችው:: የለም ይህቺ አትሆነኝም ላም ናትና ብሎ ሰይሞ ላካት:: ላም ማለት ቀንዳም ተዋጊ ማለት ነው:: (የራሴ ፍቺ ነው:: ) ደሞ ውሻ ረዳቱ ትሆን አትሆን ለማወቅ ውሻን አስጠጋት:: ውሻ ምንም ጥሩ ባህሪ ቢኖራት ውሻነቷ ሁሌ በውስጧ ነው:: የከፋት ቀን የምትዘለዝልበት ጥርስ አላት:: አትሆነኝም ውሻ ናትና ብሎ ላካት:: ድመትም ጥፍሯ አስቸጋሪ ነው:: ቀጭኔም ብትሆን ቁመቷ ዝሆንም ቢሆን ክብደቱ ጅብም ሆዳምነቱ . . . ብቻ ሁሉም የሚሆኑ አይደሉም:: ስለዚህ አዳም ለሁሉም ስም ከማውጣት ውጪ እንደርሱ ያለ የሚመች ረዳት አላገኘም::
(አዳምም ለእንስሳት ሁሉ፥ ለሰማይ ወፎችም ሁሉ፥ ለምድር አራዊትም ሁሉ ስም አወጣላቸው፤ ነገር ግን ለአዳም እንደ እርሱ ያለ ረዳት አልተገኘለትም ነበር። ዘፍ 2:20)
ምናልባት ከጋብቻችን በፊት ብዙ ሰውን እየቀረቡ ማወቅ (በጸባይ ብቻ) ትክክል የሚሆነው ለዚህ ይመስለኛል:: ቢጤያችንን ለመፈለግ በምንሰናዳበት ወቅት በመንገዳችን ላይ እንደ ላም የምትዋጋ እንደ ውሻ የምትናከስና እንደ ድመት የምትቧጭር ሴት ልታጋጥም ትችላለችና:: ያ የግድ ነው:: ትክክለኛዋ ረዳት እስትገለጥ ግን ስም እያወጣን ብቻ ።መሸኘታችን የግድ ነው:: ሜሪ ድመታዊ ፍጡር ከሆነች (የሚቧጨር ባህሪ ካላት) ስንተዋት ስም አውጥተን ነው:: ድመት ብለን:: አልማዝ ተናካሽ ከሆነች ውሻ ብለን:: ትርንጎ ተዋጊ ከሆነች ላም ናት ብለን:: ከባህሪ አንጻር ነው እንግዲህ:: ምክንያቱም በጓደኝነት ወቅት የሰውን ትክክለኛ ባህሪን ማወቅ ስለሚቻል::ይሁን እንጂ አንዳንዱ አዳም ሔዋኑ እስክትገለጥ መታገስ አቅቶት ለሚገጥሙት እንስሶች ሁሉ ስም እያወጣ መመለስ ሲችል ከዚያ አልፎ ላም አግብቶ ዘመኑን ሙሉ ሲወጋ ይኖራል:: አንዳንዱም ድመት አግብቶ ዕድሜ ልኩን ሲቧጨርና አንዳንዱ ደሞ ጅግራ አግብቶ ሕይወቱ ሰዶ የማሳደድ ሊሆን ይችላል:: አህያም የሚያገባ እንዲያ ነው። ዕድሜ ልኩን መረገጥ ነው ዕጣ ፈንታው። (ምሳሌያዊ አነጋገር ነው ደሞ ሆሆ. . . ወደ አዳም እንመለስ)
3. የምትረዳ አጥንት
እግዚአብሔር ከአዳም እኩል የፈጠራት ሴት ነገር ግን በወንድ ውስጥ የሰወራት ሴት መገለጫዋ አሁን እንደሆነ የሚወስነበት ሰዓት መጣ:: ስለዚህ እግዚአብሔር አዳም ጥልቅ እንቅልፍ እንዲወስደው አደረገ:: ይሄን ሀሳብ ብዙ የጋብቻ አስተማሪዎች እግዚአብሔርን በጸሎት መጠበቅ ማለት ነው ብለው ሲያስተምሩ እሰማለሁ:: እንቅልፍና ጸሎት ምን አንድ እንደሚያደርጋቸው ግን አላውቅም:: ሊሆን ይችላል::
(እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፥ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው። ዘፍ 2:21)
አዳም በእንቅልፍ ላይ ሳለ በአዳም ውስጥ የደበቃትን ሴት እግዚአብሔር ገለጣት:: መጽሐፉ እግዚአብሔር ከአዳም ጎን የወሰደው አንድ አጥንት ነው ይላል:: የወንድ የግራ ጎኑ ከቀኙጋ እኩል አይደለም ይባላል:: ሳይንስ ያረጋግጠው አያረጋግጠው እንጃ:: ግን እግዚአብሔር ያቺን አጥንት ሴት አርጎ ፈጠራት ይላል:: እዚህጋ የተፈጠረው ማደሪያ ነው። አስቀድማ ከአዳምጋ ለተፈጠረችው ሴት (እኔ መንፈስ ነው የምለው) መገለጫ:: አዳምምኮ ሴት አልታይ ያለችው መንፈስ ብቻ ስለሆነችበት ነው። የምትገለጥበት የስጋ ቤት ካልተሠራላት ፍፁም ሊያገኛት አይችልም ነበር። ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር በኪነ ጥበቡ ያቺን ታናሽ አጥንት ሴት አድርጎ ወደ አዳም ይዟት ይመጣል:: አቤት እንዴት ድንቅ ነው!
(እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት። አዳምም አለ፦ ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል። ዘፍ 2:22-23)
አዳምም ወዲያውኑ እንዳየ ያውቃታል:: በኔ ትርጉም ይወዳታል:: ያፈቅራታል:: ምክንያቱም በርግጥም እርሱን የምትመስለው ረዳቱ ይህቺ ናትና:: መልካም ትዳር ያላቸው ሰዎች ሲናገሩ የትዳር አጋራቸውን ሲያገኙ ወንዶቹም ሴቶቹም አጋሮቻቸውን የሚያውቁዋቸው ያህል የሚሆነው ለዚህ ይሆን እንዴ? ብዬ አስባለሁ::
ሚስት የምትገለጥ እንጂ የምትፈጠር አይደለችም:: ትክክለኛዋ ረዳታችን ከጎናችን ናት:: ከጎናችን እንድትወጣ ግን እንቅልፍ መተኛት አለብን:: እንቅልፍ ሲተረጎም ምንድን ነው? . . . እንደኔ ተዘጋጅቶ መገኘት ይመስለኛል:: . . . የምትገለጠውን ሴት ለማስተናገድ ለአቅመ አዳም መድረስ ከባዱ እንቅልፍ ነው:: አቅም ከምን ከምን አንጻር? . . . ከብዙ ነገር አንጻር:: ዋነኛው ግን ከዕድሜና አካል መደርጀት አንጻርና ከስነ ልቡና ብቃት አንጻር ነው:: ሌላው ተጨማሪ ነው::
ተፈጠመ።
ራስ ዳ. እንደጣፈው
ጁላይ 6/2017
ሲልቨር ስፕሪንግ፣ ሀገረ ማርያም
Posted in AK 3:16, የክርስቲያን ማስታወሻ- Christian Diary, Backlog - ማህደረ ጉዞ, Church - ቤተክርስቲያን, Essay-ወግ, Family - ቤተሰብ, Gospel - ወንጌል, Identity - ስብዕና, Marriage - ትዳር | Leave a comment

ዝሆን የሚመስለው ዝሆንን ብቻ ነው

(C) ዳዊት ወርቁ

elepahnt

ዝሆን የሚመስለው ዝሆንን ነው
====================
(C) ዳዊት ወርቁ
==========
ዴዜዴራታ ላይ አንድ ገራሚ አባባል አለ:: እንዲህ ይላል:- “ከሞኞችም ቢሆን ቁምነገር አይጠፋምና አዳምጣቸው::”
በሕይወትህ ምን ዓይነት ሰው ትወዳለህ ተብዬ ብጠየቅ ጸጥ ብሎ የሚያደምጥ ሰው ነው መልሴ:: አለ አይደል ስታወራ በዝምታ ጭንቅላቱን እየወዘወዘ እህ . . . እያለ ሳያናጥብህ እልህን የሚያስጨርስህ አድማጭ? . . .
ብዙ ጊዜ ግን ብዙዎቻችን እናወራለን እንጂ አናደምጥም:: ወይም እንሰማለን እንጂ አናደምጥም:: ሰውዬው ለማለት የፈለገውን ሳይሆን እኛ ለመስማት የምንፈልገውን ከንግግሩ እንይዛለን:: ከዚያም ከሰውዬው ሃሳብ ጋር ተላልፈን ቁጭ እንላለን::
አንዳንዱ የሱ ብቻ እንዲሰማ ከመፈለጉ የተነሳ የወሬ ዕድል አይሰጥህም:: እሺ ይሁንልህ ብለህ እያደመጥከው እንኳ በክርኑ እየጎሸመ እያዳመጥከኝ ነው አይደል? ይልሃል:: አዎ ቀጥል ስትለው ምን ላይ ነበርኩ? ብሎ ወሬውን እንድታስታውሰው ግድ ይልሃል:: ይሄ ሁሉ ለምላስ እንጂ ለጆሯችን ስፍራ ስላልሰጠን ነው:: ማውራት ማውራት ማውራት . . . አንዳንድ ሰዎች እግዜር ሁለት ጆሮ አንድ አፍ ያበጀልን ብዙ እንድናዳምጥ ጥቂት እንድናወራ ነው ይላሉ:: ትክክል ነው::
ሶስት ዓይነ ስውራን ዝሆንን ለመጀመሪያ ጊዜ ሊያሳዩዋቸው ወደ ጫካ ይዘዋቸው ሄዱ አሉ:: ከዚያም ላንደኛው ዓይነሥውር የዝሆኑን ጥርስ እያስነኩት ዝሆን ማለት ይህ ነው አሉት:: ለሁለተኛው ደግሞ ጭራውን እያስጨበጡት ዝሆን ይሄ ነው አሉት:: ለሶስተኛውም ጆሮውን እያስያዙት ዝሆን እንዲህ ነው አሉት::
ደሞኮ የሚወራው ወሬ ተጨባጭ ቢሆን ያባት ነው:: ከመቶ አብዛኛው እጁ አሉባልታ ነው:: የሰሚ ሰሚ ነው:: ወደ ወሬው ምንጭ ቀርበህ ነገሩን ብታጣራ ጉዳዩ አራምባና ቆቦ ሊሆን ይችላል:: ማጣራት የሚባል ነገር የለም:: ወሬ ወዳጆች እና ለወሬ ችኩሎች በሕይወት ያለውን ሰውዬ ሞተ ብለው መርዶ ሊያረዱ ይችላሉ:: የቀድሞው ዝነኛ አትሌታችን ምሩጽ ይፍጠርን ያስታውሷል::
በኋላ ሶስቱም ዓይነ ስውራን ዝሆን እንዴት አይነት ፍጡር ነው? ተብለው ሲጠየቁ::- የመጀመርያው የዝሆኑን ጥርስ የነካው ዝሆን ማለት እንደ ቀንድ የጠነከረ ፍጡር ነው አለ:: ሁለተኛው ጭራውን የጨበጠው ዝሆን የሆነ ጸጉር መሳይ ፍጥረት ነው አለ:: ሶስተኛው ጆሮውን የዳሰሰው ደግሞ የለም ዝሆን ቆዳ መሳይ ፍጥረት ነው አለ::
ብዙዎቻችን እንደነዚህ ዓይነ ስውራን ነን:: ጎዶሎ አሳብ ይዘን ስለሙሉ ነገር እናወራለን:: የሆነ ነገር ላይ እስከመጨረሻው ሄደን ሳይሆን ገና ከመነሻው ድምዳሜ ስንሰጥ እንገኛለን:: አይተን ሳይሆን ሰምተን እንፈርዳለን:: ህጻናት በዚህ ይበልጡናል:: እሳት ነው እያልናቸው እሳቱን ካልነኩት አያምኑም:: ተው እፉ ነው ያቃጥልሃል ብትለው አንድን ህጻን አይገባውም:: እሪሪሪ ካልነካሁት ብሎ ያለቅስብሃል::
ከስሜት ህዋሶቻችን ሁሉ ለጆሯችን እናደላለን:: ይሄ እንኳ የሴቶች ተፈጥሮ እንደሆነ ነበር የማውቀው:: ሴቶች ከአይናቸው ይልቅ ጆሯቸውን ያምናሉ ይባላል:: ወንድ አይቶ ሴት ሰምታ ታፈቅራለች ይባላል:: ሲጠላም ወንድ ባይኑ አይቶ ነው:: ሴትም በጆሮዋ ብቻ ሰምታ ትጠላለች ይላሉ:: ይላሉ ነው እንግዲህ:: ማኅበረሰቡ የሚያወራው ነው:: ጥናት ይሻ እንደሆን አላውቅም::
ብዙ ጊዜ አዲስ ነገር ይዘው ወደ ማኅበረሰቡ ለመቀላቀል የሚሞክሩ ሰዎች አቤት መከራቸው መብዛቱ:: ዛሬ እንዲህ ህይወታችንን ያቀላጠፈልን ቴክኖሎጂ እዚህ ያደረሱት ሰዎች ከማኅበረሰቡ የደረሰባቸውን ውጉዝ ከመአርዮስ ቤት ይቁጠረው::
ለመጀመሪያ ጊዜ መኪና ኢትዮጵያ ውስጥ ሲገባ ቀሳውስቱ አጼ ሚኒሊክን መቶበላ የሰይጣን ሥራ ነውና እንዳይገቡ ግድ ብለዋቸው ነበር አሉ:: ሀገሬው ያቺን መኪና መቶበላ ያላት መኪናዋ ሰዎችን ይዛ እብስ ስትል አይቶ ነው ይላል ጳውሎስ ኞኞ በአጤ ሚኒሊክ መጽሐፉ::
ትዝ ይለኛል ደረጀ ከበደ (ዶክተር) ቁጥር 8 የዝማሬ አልበሙን የሠራ ጊዜ ዘፈን አወጣ ተብሎ ሰዎች ካሴቱን እንዳይገዙ ተሞክሮ ነበር:: ዘማሪው ዘፈን አወጣ የተባለው ዝማሬን በዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያ ባልተለመደ የአዛዚያም “ስታይል” ይዞ በመቅረቡ ነበር:: በኋላ ግን ከደረጀ በባሰ ሁኔታ የዝማሬው ዓለም የሙዚቃውን ኢንደስትሪ ጥሶ ሲወጣ ታዝበናል:: እንዲያውም ደረጀ ቁጥር ዘጠኝ አልበሙን የሙዚቃ ደረጃውን ባልጠበቀ ሁኔታ ሲለቅ (እንደ ባለሙያዎቹ ትችት) ደረጀ አበጀ ወይስ አረጀ? ብለው በነካ አፋቸው ወርፈውታል::
የጊዜ ጉዳይ እንጂ አዲስ ነገር ሁሉ መለመዱ የተጠላው ሁሉ መፈቀሩ አይቀርም::
ለማንኛውም ብዙ ከማውራት ብዙ ማድመጥ በሩቅ ከማየት ቀርቦ መመልከት ይብዛልን:: ዝሆኑም አጥንት አይመስልም ጭራም አይመስልም ቆዳም አይመስልም ዝሆን የሚመስለው ዝሆንን ብቻ ነው::
ጤና ይስጥልኝ::
Posted in AK 3:16, የክርስቲያን ማስታወሻ- Christian Diary, ጊዜው - The Time, Backlog - ማህደረ ጉዞ, Church - ቤተክርስቲያን, Essay-ወግ, Hope - ተስፋ | Tagged , , | Leave a comment

ሐይሉ ዮሐንስ ኢትዮጵያዊው ጳውሎስ

hailu(C) ዳዊት ወርቁ
===========
ሐይሉ ዮሐንስን ለመጀመርያ ጊዜ ያወቅሁት ዩቲዩብ ላይ በሚለቃቸው ቪዲዮዎቹ ነው:: በእርግጥ ይህ ሰው የስህተት ትምህርት አስተማሪ ነው ተብዬ ነበር ስህተት ፍለጋ ቪዲዮዎቹን ማየት የጀመርኩት:: ዩቲዩብ ላይ አንድም ሳይቀረኝ ቪዲዮዎቹን አየሁ:: እውነታው ግን የበለጠ ስህተት በፈለግሁ ቁጥር ብዙ የማላውቀውን እውነት አገኘሁ::
ሐይሉ በተለይም ሰው መንፈስ ነው ነፍስ አለው በስጋ ውስጥ ይኖራል በሚለው ትምሕርቱ ይታወቃል:: በርግጥ ይህን ትምሕርት ከሱ ከመስማቴ በፊት የኬኔት ሐጌይን መጽሐፍና ቪዲዮዎች ደግሞም የዶክተር ማይለስ መጻሕፍትን ስዳሥስ የገባኝ እውነት ነው::
በእርግጥም ኢትዮጵያ ውስጥ ከማውቃቸው የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች እንደ ሐይሉ ዮሐንስ አይነት ተንታኝ አለ ማለት ያዳግተኛል:: የሚናገረውን ያውቃል:: አተናተኑ ግምታዊና ሎጂካዊ ሳይሆን በመረጃ የተመረኮዘ አሳማኝ ነው:: አንድን እውነት ለማስረዳት ሲንተባተብ አይውልም:: እንደ ብዙዎቹ ሰባኪያን ትከናወናለህ ትበዛለህ አይነት ስብከት አይሰብክም:: መጽሐፍ እየተነተነ ያስተምርሃል እንጂ:: የሚገርመኝ ይህን ሰው በአካል አላውቀውም:: የሚያስተምርበት ቦታም ሄጄ ትምሕርቱን ተካፍዬ አላውቅም:: ቀድሞ እንዳልኩት በዩቲዩብ ቪዲዮዎቹና በፌስቡክ ላይቭ በሚያስተላልፋቸው ትምሕርቶቹ ነው የማውቀው::
ብዙ ሰዎች ግን ይቃወሙታል:: ምኑን እንደሚቃወሙት ግን አይገባኝም:: ምክንያቱም ይህ ሰው መጽሐፉን ነው የሚተነትነውና:: ከማንም በላይ ስለ አዲሱ ማንነትህ አብጠርጥሮ ይነግርሃል:: እንደ ብዙዎቹ መጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ተብዬዎች አሳውን አይሰጥህም:: ግን አሳውን እንዴት ማጥመድ እንደምትችል ያሳይሃል:: ጎበዝ ነው:: ለሚጠየቀው ሁሉ መልስ አለው::
ቤቴልሔም የተባለችው የኤክዞዶስ ሾው አዘጋጅ በጋጠወጥ ባህሪዋ ልታሸማቅቀው ብትሞክር እንኳ ጥያቄዎቿን ብትህትና መልሶላታል:: በርግጥ ቤተልሔም ነህ የምትለውን በዚህ ሰው ትምሕርት ላይ አላገኘሁም::
የጽሑፌ ዓላማ ሐይሉን በከንቱ ውዳሴ ለማንቆለጳጰስ ሳይሆን ሰዎች ሁሉ ትምሕርቱን ቢያዩ ተጠቃሚ ይሆናሉ ከሚል የዋህ ምክንያት ነው:: ለዚህም ነው ሐይሉ ላይቭ ቪዲዮዎች በለቀቀ ቁጥር ብዙ የፌስቡክ ወዳጆቼን ከድንቅ ትምሕርቱ ይቋደሱ ዘንድ የምጋብዘው::
እንዲያም ሆኖ ሐይሉ የምነቅፍበት ነገር አለ:: ላይቭ ቪዲዮዎቹን ሲሰራ ብዙ ጊዜ እኔ እኔ እኔ የሚል ነገር ያበዛል:: የኔ ትምሕርት የኔ መገለጥ የኔን እንትን ኮርጃችሁ ምናምን የሚለው ነገር አለ:: ኮመንት ላረገው ሞክሬ ነበር:: ሰዎች የኔን ትምሕርት እየኮረጁ አትበል:: ታዲያ አላማህ ምንድነው? ትምሕርትህ እንዲኮረጅ ካልፈልክ ብዬዋለሁ:: መልስ ባይሰጠኝም::
ትምሕርቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው:: እሱ ከየትም አላመጣውም:: ግን ከመጠን በላይ በራሱ ይመካል:: ይሄ ደግሞ የትም አያስኬደውም:: አያሳድገውም:: ባለበት ከመርገጥ ውጪ::
ሌላው የታዘብኩት በላይቭ ቪዲዮዎቹ በብዛት ስለሰዎች ያወራል:: ስለሚቃወሙት:: አንዳንድ ጊዜ ጊዜውን ስለነዚህ ሰዎች ሲያወራ ጣፋጭ ትምሕርቱ አየር ላይ ባክኖ ያልቃል:: ይሄንንም ቢያርም ደስ ይለኛል::
በተረፈ ሐይሉ የዘመኑ ኢትዮጵያዊ ጳውሎስ ብዬዋለሁ:: ድንቅ አስተማሪ ነው::
ሌሎቹ ሰባኪያን የምናውቀውን እውነት አጣፍጠው አሊያም አጋነው እየኮመኩ ወይም እያስፈራሩ ይሰብኩናል:: ይህ ሰው ግን ተራ በሆነ ንግግር የማናውቀውን እውነት ያስተምረናል::
ወንድሜ ከዚህ በላይ ያብዛልህ::
Posted in AK 3:16, የክርስቲያን ማስታወሻ- Christian Diary, Backlog - ማህደረ ጉዞ, Church - ቤተክርስቲያን, Gospel - ወንጌል, People-ሰዎች | Tagged , , , , | 2 Comments

የአዲስ ኪዳን ነቢያት አሳዳጆች

(C) ዳዊት ወርቁ
============
 2009summer_the-new-testament-rightly-divided-or-torn-apart_1920x1080_1

የዛሬ ዓመት አካባቢ ነው:: አንድ ስመ-ጥር ነቢይ እኔ እኖርባት ከነበረች ከተማ ከሚገኝ አንድ የሐበሻ “ቸርች” ሊያገለግል ከኢትዮጵያ ተጋብዞ መጣ:: በዚያች ከተማ ምንም እንኳ ጥቂት ሐበሾች ቢኖሩም ነገር ግን ቢያንስ ከ5 በላይ ትንንሽ ቸርቾች ነበሩ:: በያንዳንዱ ቸርች ውስጥ የሚያመልከው ሐበሻ በቁጥር እጅግ በጣም አናሳ ነው:: ቢጠራቀም አንደኛውን ቸርች እንኳ መሙላቱን እንጃ:: ግን ታዋቂው ነቢይ መጣ የተባለ ቀን አገልጋዩን የጋበዘው ቸርች መላወሻ እስኪታጣ ድረስ ካፍ እስከ ገደፉ ጢም አለ:: ምክንያቱ አንድና አንድ ነው:: አገልጋዩ ነቢይ ነው ስለተባለ::

ነቢዩ (ስሙን ብጠራው ምን ችግር አለው ግን?) ምንም:: ነቢይ መድኅን ነው:: ከሙሉወንጌል ቸርች:: ይህ ሰው ታዲያ እንዲህ ነው ያደረገው:: ጉባኤውን ቢመለከት ሰው ሁሉ አሰፍስፎ አንዳች ነገር ይጠባበቃል:: ትንቢት:: ስለዚህም እንዲህ አለ:: ይቅርታ አርጉልኝ ዛሬ እዚህ የተገኘሁት ልሰብክ እንጂ ልተነብይ አይደለም:: እግዚአብሔር ይባርከው:: ጌታን ሳይሆን ትንቢት ፍለጋን አሰፍስፎ የመጣውን ኩም አርጎ መለሰው:: ጠብታ ትንቢት ሳያመጣ ጉባኤው ተጠናቀቀ::

በብሉይ ኪዳን ዘመን ሰዎች ነቢያትን ቢያሳድዱ ከእግዚአብሔር ቁጣ ያመለጡ መስሏቸው ነው:: ምክንያቱም ነቢያት የእግዚአብሔር አፍ ስለነበሩ እግዚአብሔር ከሕዝቡጋ ጉዳዩን የሚጨርሰው እነሱን እየተጠቀመ ነበርና:: እግዚአብሔር ለሕዝቡ ተግሳጽ ቢያመጣ በነቢያቱ ነው:: ፍርድ ቢሰጥ በነቢያቱ ምክር ቢለግስ በነቢያቱ ቁጣውን ቢያመጣው በነቢያቱ . . . ነው::

ዛሬ በአዲስ ኪዳን ዘመን ግን እንዲያ አይደለም:: እግዚአብሔር ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ባመንን ጊዜ በተቀበልነው መንፈስ ቅዱስ አማካይነት እንጂ ነቢያትን አይጠቀምም:: መጠቀምም የለበትም:: አይ ነቢያት እንደ ብሉይ ኪዳን አገልግሎት እየሰጡ ነው ከተባለ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ምንም ሊሆን ነው:: (የነቢያት ቢሮ አለ የለም በሚለው ላይ አይደለም አሳቤ) በአዲስ ኪዳን ላይ ያየንም እንደሆነ ሐዋርያቱ ሥራቸውን ይሰሩ የነበሩት በቀጥታ ከመንፈስ ቅዱስ ድምጽ እየተቀበሉ እየሰሙ እንጂ ነቢያትን እያሳደዱ አልነበረም::

እንዲያም ሆኖ ዛሬ ዛሬ እኛ የአዲስ ኪዳን ነቢያት ነን የሚሉ ሰዎች ይሰደዳሉ። አሳዳጆቻቸው ዳግም የተወለዱ ክርስቲያኖች ናቸው:: የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ መስማት የተሳናቸው አማኞች ናቸው:: ጆሮዋቸውን ለነቢያት እንጂ ለጌታ ዝግ ያደረጉ ሰዎች ናቸው::

በእርግጥ የአዲስ ኪዳን አማኞች ነቢያትን የሚያሳድዱት ሊያጠፏቸው ሳይሆን ሊያለሟቸው ነው:: እግዚአብሔር በነሱ አድሮ ምን ተናገረኝ የሚለውን ለመስማት ነው:: ማሳደዱ ከጥላቻ የመጣ ሳይሆን ከውዴታ ነው:: ማሳደዱ ለጉዳት ሳይሆን ለመፍትሔ ነው::

በርግጥም ያ ክፉ አይደለም:: ክፋቱ ነቢያትን ባሳደድን ቁጥር ሳናውቀው መንፈስ ቅዱስን ከውስጣችን እያሳደድነው መሆኑ ላይ እንጂ:: መንፈስ ቅዱስ ሊናገረን ይፈልጋል ሁልግዜ:: እኛ ግን ድምጹን መለየት ስላልቻልን ነቢያት እናሳድዳለን:: ግና ነቢያቱጋ ያለው ያው መንፈስ እኛምጋ ነበረ:: ምን ያህሎቻችን ይሆን ይህ ሚስጥር የገባን? . . . እኔ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ካለ ለከበበኝ ችግር ውቅያኖስ አቋርጬ ነቢይ የማሳድደው ለምንድነው? . . . እኔ በበኩሌ መንፈስ እኔን አልፎ ለዚያ ሰውዬ ስለኔ የሆነ ነገር ካለው የሆነ ቦታ ችግር አለ ማለት ነው:: ወይ እኔጋ ወይ ሰውዬውጋ

ብዙ ነቢያት ነን የሚሉ ሰዎች ካለባቸው ስደት ጫና የተነሳ ብዙ ጥፋት የሚያጠፉትም ለዚህ ነው:: አብዛኛዎቹ የተሳሳተ ድምጽ እየሰሙ ወደ አሳዳጆቻቸው ያቀብላሉ:: አሳዳጆቻቸው የመጣላቸውን የተሳሳተ ድምጽ ይዘው ሲጠብቁ በባዶ ተስፋ ከሕይወት መንገድ ይስታሉ:: ብዙዎቹ በስጋም በመንፈስም ተጎድተዋል:: እዚህ ብናነሳው በጎ ላይሆን ይችላል በሚል እንተወው እንጂ ብዙ አማኞች በመንፈስም በስጋም ኪሳራ ደርሶባቸዋል::

በብሉይ ኪዳን ጊዜ እግዚአብሔር ነቢያቱን ይጠቀም የነበረው ብቸኛ ሕዝቡን የማግኛ መንገዶች ስለነበሩ ነው:: ዛሬ ግን እግዚአብሔር ሕዝቡን መናገር ከፈለገ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይልሃል የሚል ነቢይ የሚያስፈልገው አይመስለኝም:: ምክንያቱም ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ለተቀበሉ ሁሉ አብሮ የሚሰጠው መንፈስ ቅዱስ አለንና:: በሌላ አማርኛ ራሱ እግዚአብሔር በውስጣችን አለና ነቢያት አያስፈልጉንም ብዬ በድፍረት እናገራለሁ::

ምናልባት እግዚአብሔር ሌሎች ሰዎችን (ነቢያትን) ከኛ አልፎ የሚጠቀምበት ጊዜ ቢኖር በሁለት ምክንያቶች ይመስለኛል::

1ኛ. በተደጋጋሚ ለራሳችን በሚገባን መንገድ ያስለመደንን ድምጽ ቸል ባልን ጊዜ ወይም አልሰማ ባልን ጊዜ

2ኛ. ለተናገረን ድምጽ (ብዙ አይነት ድምጽ ስላለ) የራሱ ድምጽ መሆኑን ሊያረጋግጥልን በሚፈልግ ጊዜ

ዛሬ ዛሬ አንድ ቸርች በሰዎች ጢም ቢል አትገረም እዚያ ቦታ ነቢይ አለ ማለት ነው:: ዩቲዩብ ስከፍት ኢትዮጵያ ውስጥ በነቢይ አገልግሎት የተነሱ ሰዎችን አያለሁ:: ቸርቻቸው ለጠጠር መጣያ ቦታ የለም:: ሰው ሁሉ ለእንቆቅልሹ ከያለበት ተከማችቷል:: ከዚያ ሁሉ ወፈ ሰማይ ጥቂቱ መልስ አግኝቶ ይመለሳል:: አብዛኛው ከነተግዳሮቱ አንገቱን እንደደፋ ይመለሳል:: እንዴት ያሳዝናል!

ቃሉ በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እነርሱም ይከተሉኛል ካለ እንዴት ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ተላለፍን?

ትዳርን የሚያህል ነገር ካንቺ ከባለቤቱ አልፎ በነቢይ እገሌ ስም አግቢው አሊያም ፍቺው የሚል ድምፅ ከመጣ ከጌታ ሳይሆን ከሰው ነው ።

ምንድነው ችግሩ? . . . ጌታ ለምንድነው እኛን ያለፈን? . . . የችግሩ ባለቤቶች እኛን ትቶ ለሌላ ሰው ሚስጥራችንን መግለጥ ለምን ፈለገ ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ:: መልሼም ለራሴ መልስ እሰጣለሁ:: ጌታን ሳይሆን ጌታ የሚጠቀምበትን ሰው ስለፈለግን ነው:: መድኃኒቱን ሳይሆን የመድኃኒቱን መያዣ ዕቃ ስለፈለግን ነው::

ይህንንም ተጠቅመው ታዲያ ብዙ ነቢይ ነን የሚሉ ሰዎች አድቫንቴጅ መቱብን:: የእግዚአብሔርን ድምጽ መስማት ስለተሳነን አጋጣሚውን ተጠቀሙብን:: እንዲህና እንዲያ ትሆኛለሽ እያሉ የሌለ ቃል ዘሩብን:: ባዶ ተስፋ መገቡን:: ከመስመር አወጡን:: ለመንፈስ ቅዱስና ለቃሉ ጊዜና ቦታ ስላልሰጠን በትምሕርት ነፋስ ሁሉ ተፍገመገምን::

እንንቃ:: የመመለስና የማረፍ ዘመን ይሁንልን:: ለእግዚአብሔርና ለቃሉ ጊዜ የመስጠት ዘመን ይሁንልን:: ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔርን ድምጽ የመለየት ጊዜ ይምጣልን:: አሜን::

 

Posted in AK 3:16, የክርስቲያን ማስታወሻ- Christian Diary, ጊዜው - The Time, Backlog - ማህደረ ጉዞ, Church - ቤተክርስቲያን, Essay-ወግ, Gospel - ወንጌል, Hope - ተስፋ, Life - ሕይወት | Leave a comment

ሰማዩን ለመንካት

– ዳዊት ወርቁ
 
(ዋይት ሃውስ ቅፅር ግቢ ከሚገኘው ሮዝ ጋርደን ዶናልድ ትራምፕ ሜይ 4 ብሔራዊ የጸሎት ቀን ሆኖ እንዲከበር ሲፈርሙ በቀጥታ ሲተላለፍ እኔ እንዲህ አስብ ነበር  . . .)
 
seekingሕዝቅያስ የተባለው የይሁዳ ንጉሥ እግዚአብሔርን መፈልግ ሲጀምር  እግዚአብሔር ሕዝቅያስን:- “ነገር ግን የማምለኪያ ዐፀዶቹን ከምድር አስወግደሃልና፥ እግዚአብሔርንም ትፈልግ ዘንድ ልብህን አዘጋጅተሃልና መልካም ነገር ተገኝቶብሃል አለው።”  (መፅሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 19:3)
 
(በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ልዕለ ኃያል በነበረችበት ጊዜ ቲርሃቅ የተባለው የኢትዮጵያ ንጉሥ ሕዝቅያስን ሊወጋ ሄዶ ነበር ይለናል መጽሐፍ ቅዱስ)
 
በሰው ዘንድ መልካም ነገር ተገኘ የሚባለው መልካም ነገር ስላደረገ አይደለም። ሐይማኖተኛ መሆንም  አይደለም:: ወይ በሃብት ሲበለጽግ:: ወይም ደግሞ ከዕውቀት ማማ ሲወጣ። ነገር ግን በሰው ዘንድ መልካም ነገር ተገኘ የሚባለው ልቡ እግዚአብሔርን ሲፈልግ ብቻ ነው::
 
ሰው እግዚአብሔርን መፈለግ ሲጀምር እጅ ሰጠ ይባላል:: ተሸነፈ ይባላል:: ከሱ በላይ ላለው ኃያል አምላክ ራሱን አስገዛ ይባላል:: እንዲያ ሲሆን ደግሞ የህይወት ምህዋር ይስተካከላል::
 
ሀገር እግዚአብሔርን መፈለግ ስትጀምር ፈውስ ይሆናል:: ጥጋብ ይሆናል::
 
በቴሌቪዥኔ መስኮት እነ ዶናልድን እያየሁ ስላገሬ አስባለሁ:: ስለ ኢትዮጵያ:: መጽሐፍ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ይላል:: (መቼ? . . . )
 
ሕዝቤ እግዚአብሔርን ይፈራል:: ልክ ነው:: ሐይማኖተኛ ሕዝብ ነው:: ሐይማኖተኝነት ማለት ግን እግዚአብሔርን መፈለግ አይደለም:: እግዚአብሔርን መፈለግ ማለት በእውነትና በመንፈስ እግዚአብሔርን ማምለክ ነው:: ቂምና ጥላቻን አስወግዶ ባልንጀራን መውደድ ነው:: ከኔ አንተ ትብስ ማለት ነው:: ከባልሽ ባሌ ይበልጣል ሽሮ አበድሪኝ የሚለውን ምሳሌያዊ አባባል በተገላቢጦሽ መረዳት ነው::
 
መንግሥታችን ከሀይማኖት የራቀ ነው:: ሐይማኖተኛን ሕዝብ የሚመራው ሐይማኖት የለሽ መንግሥት ነው:: ሕገ መንግሥቱ መንግሥት ከሃይማኖት ውጪ እንዲሆን ይናገራል (ካልተሳሳትኩ)
 
ኢትዮጵያ ከፖለቲካዊ ቀውስ: ባሻገር ረሃብ ጦርነትና በሽታ የሚፈታተናት ምስኪን ባልቴት ናት:: ፊቷን ወደ እግዚአብሔር የምትመልሰው ቅን ፈራጅ መሪዎች ሲገጥሟት ነው::
 
በቅን የሚፈርዱ መሪዎች ደሞ እግዚአብሔርን ከሚፈራ ማንነት (ልብ) ውስጥ ይፈልቃል::
 
ግፍ በምድራችን እንደተራራ ተከምሯል:: በታሪክ የሰማነው ያነበብነው:: ያየነው የምናየው ግፍ የደም ዕምባ ጽዋ ሞልቷል:: ምድራችን የሚያዋጣት አንድና አንድ ነው:: እግዚአብሔርን መፈለግ::
 
እግዚአብሔር ሲፈለግ ዝም አይልም:: ይመጣል:: መጥቶም ቋጠሮን ይፈታል:: ተራራውን ይንዳል:: ስርጓጉጡን ያስተካክላል::
 
አሜሪካ ሃያል ናት:: ጉልበተኛ:: ምድራችንን ግንባር ቀደም ሆና ትመራለች:: አሁን ግን ተሸነፈች:: ተንበረከከች:: እግዚአብሔርን ፈልጋለችና::
 
ኃያል አገር አሜሪካ ፈጣሪን ከፈለገች ኢትዮጵያማ እንዴት? . . .
 
ዶናልድ ትራምፕ ሚስጥሩ የገባቸው ይመስላሉ:: በርግጥም ስለምክትላቸው ፔንስ ሲናገሩ በእምነቱ ጥልቅ የሆነ ካሉ በኋላ ከርሱጋ በመሥራቴ ዕድለኛ ነኝ ብለዋል ከነጩ ቤተመንግሥት በቀጥታ ሲተላለፍ በነበረው ብሔራዊ የጸሎት ቀን ሥነ-ስርዓት ላይ::
 
እግዚአብሔርን መፈለግ ሞኝነት ሳይሆን ብልጠት ነው:: እግዚአብሔርን ስንፈልግ ታሪክ አያጣላንም:: ምክንያቱም ምድራዊ ታሪክ ወንዝ እንደማያሻግር ስለሚገባን:: እግዚአብሔርን ስንፈልግ እኛን የሚፈልገን ጠላት ጭራውን ሸጉቦ ይወጣል::
 
ኢትዮጵያ ከገባችበት የፖለቲካ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ቀውስ የምትወጣው እግዚአብሔርን ስትፈልግ ብቻና ብቻ ነው:: እግዚአብሔርን ስንፈልግ ሁላችንም ያንድ አባት ልጆች እንደሆንን እንረዳለን:: ወንድማማችና እህትማማቾች:: አዎ ያኔ ፍቅር ይሆናል:: ፍቅር እግዚአብሔር ነውና:: እግዚአብሔርን መፈልግ ማለት ጉልበትን ማንበርከክ ነው:: ጉልበት ሲንበረከክ ሰማይ ይነካል::
 
(I touch the sky when my knees hit the ground. እንድትል ዘማሪዋ::)
Posted in AK 3:16, የክርስቲያን ማስታወሻ- Christian Diary, Backlog - ማህደረ ጉዞ, Church - ቤተክርስቲያን, Essay-ወግ, Gospel - ወንጌል, Hope - ተስፋ, Life - ሕይወት, Love - ፍቅር | Tagged , , , , , | Leave a comment

በሽታ በአማኝ ላይ የእግዚአብሔር አዠንዳ ነውን ?

– ዳዊት ወርቁ
 
docሁለት አይነት አመለካከት እሰማለሁ ስለበሽታ:: የመጀመርያው:- አማኝ እንደማንኛውም ሰው በሽታ ይጎበኘዋል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የለም በፍጹም የሚል::
ሁለቱም ጎራ ከመጽሐፍ ማስረጃ እየመዠረጠ ይነታረካል::
 
አንተ የቱጋ ነህ? ካላችሁኝ ሁልግዜ ጥሩጋ መሆን እፈልጋለሁ:: ጥሩው ደግሞ አማኝን በሽታ አያጠቃውም ነው:: ልብ አርጉ እኔምጋ በርካታ ጥቅሶች አሉ:: ግን አሁን የጥቅስ ጨዋታ አይደለም ጉዳዩ:: ጉዳዩ የአካሄድና የመረዳት ደሞም የመድረስ ነው::
 
አንዱ ተነስቶ በሽታ አማኝን ማጥቃት የለበትም ቢል ማስረጃ ማቅረብ ከቻለ የቱጋ ነው ችግሩ? . . . እንዲያውም አሪፍ አይደል እንዴ? ተገኝቶ ነው ብሎ ጆሮ ማዋስ ሲገባ የለም ይሄ የሐሰተኞች ትምህርት ነው እንዲያ ነው አይባልም::
 
አማኝን በሽታ ሊያጠቃው አይችልም ካለ መልሱ ጥሩ ነው ብራዘር እንደ እምነትህ ይሁንልህ ነው:: አንተ አማኝ ነህ ግን በሽታ እንደሚጎበኝህ ታምናለህ:: ያኛው አማኝ ደግሞ የለም በሽታ አይዘኝም ካለ እንደ እምነትህ ይሁንልህ ነው የሚባለው::
 
(ስማርት ከሆንክ ኮርጀው:: እንዴት ጤነኛ መሆን ቻለ? . . . አንተም እሱም አንድ አምላክ እያመለካችሁ እንዴት እሱ ጤነኛ አንተ በሽተኛ ሆንክ? . . ዊርድ ነው:: ስለዚህ የሆነ የደረሰበት ነገር አለ ማለት ነው:: ታዲያ ለምን አትጠይቀውም ሐሰተኛ መምህር ነው እያልክ ከምትኮንነው? . . . ነው ወይስ በሽታ አሪፍ ነው? . . . እሱን አንተ ታውቃለህ::)
 
አሁን ችግሩ ጥቅስ አይደለም:: ከላይ ከጽሑፌ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ብዙ ጥቅሶች አሉ:: ይሄንንም ሆነ ያንን የሚደግፉ:: ቁምነገሩ መረዳቱ ላይ ነው:: ልዩነቱ ያ ከሆነ አንተ ትታመማለህ በሽተኛ ትሆናለህ እያልክ ጥቅስ ከምትጠቅስብኝ ይልቅ በሽተኛ አትሆንም እያለ ጥቅስ እየጠቀሰ የሚያስተምረኝን እመርጣለሁ:: ያ መረዳት ለኔ ትልቅ ስለሆነ:: ተስፋ ስላለበት:: ሕይወት ሕይወት ስለሚሸት:: ያኛው ግን ባዶ ተስፋ ነው:: በሽታ አለበት:: ሞት አለበት:: አያንጽም:: ምንም ደጋፊ ጥቅስ ቢኖር ማለቴ ነው::)
 
በርግጥም ማስተማርስ በሽታ የእግዚአብሔር አዠንዳ እንዳልሆነ ነበር:: መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር በሽታ ለግብጻውያን በቅጣት መልክ የመጣ መአት ነው:: (ዘጸአት 15 26 አብረን እናንብብ እንዲህ ይላል)
 
“አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ፥
በፊቱም የሚበጀውን ብታደርግ፥
ትእዛዙንም ብታደምጥ፥
ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ፥
በግብፃውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፤
እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና አለ።”
 
እውነቱ ይህ ነው::
 
ወዲህ ግን በርካታ አማኞች በበሽታ ይጠቃሉ:: ጉንፋኑ አስሙ ራስ ምታቱ ቁርጥማቱ ጨጓራው ሳምባው . . . ኧረ ምኑ ቅጡ!! . . .
 
ለምናስተምረው ነገር “ሪፈረንስ” ሊኖረን የግድ ነው:: የኛ ትልቁ ሪፈረንሳችን ኢየሱስ ነው:: ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ ሲመላለስ እንዲህ የሚባል በሽታ ይዞት ነበር የሚል ነገር እስካሁን አላነበብኩም አልሰማሁምም:: እዚህጋ አንዳንድ ሰው ኢሳያስ 53ን ጠቅሶ እንዴ “የሕማም ሰው” ነው ይላል ብሎ ኢየሱስ ታማሚ እንደነበር ማስረጃ ሊያቀርብ ይሞክር ይሆናል:: የሕማም ሰው ማለት በሽተኛ ማለት ነው እንዴ? . . . በፍጹም አይደለም:: a man of sorrows ይላል የእንግሊዘኛው አቻ ትርጉም:: እኔ በሐዘን ላሉ ቅርብ ብዬ ተረድቼዋለሁ::
 
ይልቅዬ መጽሐፉ የሚነግረን ስለ ኢየሱስ በሽተኛነት ሳይሆን ኢየሱስ በሽተኞችን እንደፈወሰ ነው:: በተመሳሳይ ቋንቋ አሁንም መጽሐፉ የሚነግረን አማኞች እጆቻቸውን በበሽተኞች ላይ እንደሚጭኑና በሽተኞቹም እንደሚፈወሱ እንጂ በበሽታ ቁም ስቅል እንደሚያዩ አይደለም::
 
የወንጌልን አደራ ከኢየሱስ የተረከቡትም ሐዋርያት በበሽታ እየተሰቃዩ ሐኪም ፍለጋ ሲራወጡ አላነበብኩም:: የማስታውሰው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ለሆድህ ህመም ጥቂት የወይን ጠጅ ተጎንጭ ያለውን ነው:: ያም ቢሆን ይህ ጥቅስ በሽታ በአማኝ ላይ እንደማይሠራ የሚያስረዱትን ጥቅሶች ፉርሽ አያደርገውም::
 
እንግዲያውስ ለምን እንታመማለን? . . . እንጃ:: ያልደረስኩበትን ልጽፍ አልደፍርም:: የደረሳችሁበት ካላችሁ አንዳች በሉ::
ጤና ይስጥልኝ::
Posted in AK 3:16, የክርስቲያን ማስታወሻ- Christian Diary, Backlog - ማህደረ ጉዞ, Church - ቤተክርስቲያን, Gospel - ወንጌል, Hope - ተስፋ, Identity - ስብዕና, Life - ሕይወት | Leave a comment