ሴት ስትገለጥ

(በተለይ ላላገቡ ወንዶች የተፃፈ)
(C) ዳዊት ወርቁ
እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት።
(ኦሪት ዘፍጥረት 2: 18)
1. ሴት ሴት ሲሸት
love-cartoon-pic-getty-images-85892412በዔደን ገነት ውስጥ አዳም ብቻውን ባይሆንም ብቸኛ ነበር:: ምን የእግዚአብሔር ኅልውና አብሮት ቢሆን ደግሞም በሰማይ ወፎችና በምድር እንሥሳት ቢከበብ አዳም ብቸኛ ነበር:: ዙሪያ ገባው ወና ነው። ሰው ሰው አይሸትም። ሴት ሴት አይሸትም። ወደ ቀኝ ዞር ሲል ስማቸውን እንኳ የማያውቃቸው እንስሶች ናቸው:: ወደ ላይ ቀና ቢል ወፎችና አሞሮች ናቸው:: ወደታች ዝቅ ቢል ተሳቢ እንስሳት ናቸው:: ወደ ግራ ቢዞር ዙሪያ ገባው አበባና ደን ብቻ ነው:: ብቸኝነቱ ልክ እሱን የምትመስል ተቃራኒ ፍጡር ስለሌለች ነው:: ሴት ስለሌለች ነው። ቢጤው ስለሌለች ነው:: ሌሎቹ እንስሳት ግን ተባዕት ከእንስት ናቸው:: ከአዳም በቀር ሁሉም ከቢጤው ነው:: አዳም ብቻውን ባይሆንም ብቸኛ ነበር:: ብቸኝነቱን ሲያስብ ምናልባት ይቆዝም ይሆናል:: ምናልባት ጸሐይ ስትወጣና ስትጠልቅ በሀሳብ ይፈዝ ይሆናል:: ተባእቱ ተ እንስቱ መላ እንስሳቱ ፍቅር ሲሠሩ ስለ ራሱ እያሰበ ግራ ይጋባ ይሆናል። ነገር ግን አዳም ብቸኝነቱን የምትጋራው ቢጤው ከጎኑ እንደነበረች በፍጹም አላወቀም:: የምታስፈልገው ሴት ሩቅ አልነበረችም። ከጎኑ ነበረች። በከባድ እንቅልፍ እስታልወደቀ ድረስ ግን አልተገለጠችም።
አንዳንዴ ብቻ ሳይሆን ሁልግዜ ህይወት እንዲያ ናት:: ያላገባንና በብዙ ሴቶች ተከበን ግራ የገባን ወንዶች ምን በሴቶች ጭን እየተደበቅን ብቸኝነትን ለማባረር ብንጥር እስታሁን ብቸኞች ነን:: ምክንያት? . . . ከከበቡን እንስት መሀል ቢጤያችን የለችማ! ስለዚህ ልክ እንደ አዳም ሴት ሴት ሊሸተን ይችላል። ሴት ምን ምን ትሸታለች? ተብሎ ቢጠየቅ ብቸኝነት ያንጠራወዘው አዳም ቀድሞ እጁን ያወጣል። ስለዚህ አንዳንድ ሰዎች በተለይም የትዳር ጓደኛ መፈለግ ያታከታቸው የኔ ሚስት ገና አልተፈጠረችም ይላሉ:: ይሄ የስንፍና ወይም ያላዋቂነት ንግግር ይመስለኛል:: ሔዋንህማ ከጎንህ ናት። ችግሩ አለመገለጧ ነው። ለምን አልተገለጠችም?. . . ምናልባት ብቸኝነትህ መልካም ይሆናል። ወይም ደግሞ ብቸኝነትህ መልካም አይደለም እስኪባል ድረስ መቆየት ይኖርብህ ይሆናል።
እግዚአብሔር በርግጥም ለአዳም ሄዋኑን መግለጥ ያለበት ሰዓት ሲደርስ ገልጦለታል:: ሔዋን ከመገለጧ በፊት ግን አዳም በከባድ እንቅልፍ እንዲወድቅ ተደርጓል:: ከዚያ በኋላ ነው ውስጡ የነበረችው ሴት የወጣችው:: ሔዋን በአዳም መሻት መሰረት የተፈጠረች ሳይሆን የተገለጠች ናት:: በነገራችን ላይ በመፍጠር ሂደት ሴት ከወንድ ቀጥሎ ሳይሆን ዕኩል ነው የተፈጠረችው::
( እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ዘፍ 1: 27)
በመግለጥ ሂደት ነው ቀጥሎ የምትሆነው:: ስለዚህ እንደ አዳም ስጋ ለብሳ በገነት ውስጥ ባትንቀሳቀስም ሴት ተፈጥራ ነበር:: በርግጥም ሔዋን በአዳም ውስጥ ሆና ትንቀሳቀስ ነበር:: ራሷን ችላ ስጋ ለብሳ የምትንቀሳቀስበት ጊዜ ግን ገና ነበር:: የመገለጥ ጊዜዋ ስላልደረሰ እግዚአብሔር አልገለጣትም:: ወይም ደግሞ መገለጧ እንደ አዳም ስሜትና ፍላጎት ይሆናል:: ምናልባት አዳም ብቸኝነቱ መልካም ቢሆንስ ኖሮ? . . . ሴት ላትገለጥ ትችል ነበር ማለት ነው? . . . አይመስለኝም:: ምክንያቱም የእግዚአብሔር ዓላማ በራሱ መልክ የፈጠረው ሰው በምድር ላይ እንዲበዛለትና ምድርን እንዲሸፍንለት ወይም እንዲሞላለት ከሆነ ሴት የግድ መገለጥ አለባት። በነገራችን ላይ እግዚአብሔር አዳምንና ሔዋንን ብዙ ተባዙ ብሎ የባረካቸው አስቀድሞ ሴት ሳትገለጥ ነው።
(እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው። ዘፍ1: 28)
ሰው መንፈስ ስለሆነ ለመባዛት ስጋ ያስፈልገዋል:: አንድ ጊዜ እግዚአብሔር ዘሩን በአዳም ውስጥ አድርጓልና:: ከዚያ በኋላ ስጋ ነው የሚቀረው:: ስጋ ደሞ ዋነኛ ጥቅሙ በቁሳዊው ዓለም ለመኖርና ብዙዎችን ለማብዛት ነው:: መንፈስ የሆነው ሰው ግን ዘሩ አንድ ነው:: ያም ዘር እግዚአብሔርን ይመስላል:: የማይባዛ የማይከለስ ዘር ነው:: መንፈስ ነውና:: በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረው መንፈስ የሆነው ሰው በቁሳዊው ምድር ላይ የሚኖርበት መኖሪያ (ስጋ) ገና አልተበጀለትም ነበር:: መንፈስ የሆነው ሰው ጾታው ሁለት ነው:: ወንድና ሴት:: በስጋ ውስጥ እስኪገባ ድረስ በአንድ ስም ሰው ተብሎ ይጠራም ነበር:: ሰው ማለት ደሞ ወንድና ሴት ማለት ነው:: ሰው = ወንድ + ሴት:: በዘፍጥረት ምዕራፍ 2 ላይ ግን ሰው ለሁለት ጾታ ይከፈላል:: ከዚያ በፊት ግን ይህ ስጋ የለበሰው መንፈስ የሆነ ሰው ረዳት እንደሚያስፈልገው እግዚአብሔር ተረዳ::
(እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት። ዘፍ 2: 18)
2. የማትረዳ ረዳት
እዚህጋ ነው የሚገርመኝ:: እግዚአብሔር ረዳት እንፍጠርለት ብሎ ለአዳም ያመጣለት ረዳት እንስሶችን ነው:: እንጂ ከአዳምጋ አብሮ የፈጠራትን ሴት አይደለም:: በርግጥ እግዚአብሔር እንስሶቹን ወደ አዳም ሲያመጣ አዳም እንደርሱ ያለ ረዳት በሚፈልግበት ሁናቴ እግረ መንገዱንም ለስም አልባዎቹ እንስሳት ስም እንዲያወጣላቸው ነው::
(እግዚአብሔር አምላክም የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉ ከመሬት አደረገ፤ በምን ስም እንደሚጠራቸውም ያይ ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው፤ አዳምም ሕያው ነፍስ ላለው ሁሉ በስሙ እንደ ጠራው ስሙ ያው ሆነ። ዘፍ 2:19)
አዳም ረዳቱ እንድትሆን ማንን አስቀድሞ እንደመረጠ ባላውቅም ነገር ግን እንገምት:: ለምሳሌ ላምን መረጠ እንበል በቀንዷ እየወጋች አስቸገረችው:: የለም ይህቺ አትሆነኝም ላም ናትና ብሎ ሰይሞ ላካት:: ላም ማለት ቀንዳም ተዋጊ ማለት ነው:: (የራሴ ፍቺ ነው:: ) ደሞ ውሻ ረዳቱ ትሆን አትሆን ለማወቅ ውሻን አስጠጋት:: ውሻ ምንም ጥሩ ባህሪ ቢኖራት ውሻነቷ ሁሌ በውስጧ ነው:: የከፋት ቀን የምትዘለዝልበት ጥርስ አላት:: አትሆነኝም ውሻ ናትና ብሎ ላካት:: ድመትም ጥፍሯ አስቸጋሪ ነው:: ቀጭኔም ብትሆን ቁመቷ ዝሆንም ቢሆን ክብደቱ ጅብም ሆዳምነቱ . . . ብቻ ሁሉም የሚሆኑ አይደሉም:: ስለዚህ አዳም ለሁሉም ስም ከማውጣት ውጪ እንደርሱ ያለ የሚመች ረዳት አላገኘም::
(አዳምም ለእንስሳት ሁሉ፥ ለሰማይ ወፎችም ሁሉ፥ ለምድር አራዊትም ሁሉ ስም አወጣላቸው፤ ነገር ግን ለአዳም እንደ እርሱ ያለ ረዳት አልተገኘለትም ነበር። ዘፍ 2:20)
ምናልባት ከጋብቻችን በፊት ብዙ ሰውን እየቀረቡ ማወቅ (በጸባይ ብቻ) ትክክል የሚሆነው ለዚህ ይመስለኛል:: ቢጤያችንን ለመፈለግ በምንሰናዳበት ወቅት በመንገዳችን ላይ እንደ ላም የምትዋጋ እንደ ውሻ የምትናከስና እንደ ድመት የምትቧጭር ሴት ልታጋጥም ትችላለችና:: ያ የግድ ነው:: ትክክለኛዋ ረዳት እስትገለጥ ግን ስም እያወጣን ብቻ ።መሸኘታችን የግድ ነው:: ሜሪ ድመታዊ ፍጡር ከሆነች (የሚቧጨር ባህሪ ካላት) ስንተዋት ስም አውጥተን ነው:: ድመት ብለን:: አልማዝ ተናካሽ ከሆነች ውሻ ብለን:: ትርንጎ ተዋጊ ከሆነች ላም ናት ብለን:: ከባህሪ አንጻር ነው እንግዲህ:: ምክንያቱም በጓደኝነት ወቅት የሰውን ትክክለኛ ባህሪን ማወቅ ስለሚቻል::ይሁን እንጂ አንዳንዱ አዳም ሔዋኑ እስክትገለጥ መታገስ አቅቶት ለሚገጥሙት እንስሶች ሁሉ ስም እያወጣ መመለስ ሲችል ከዚያ አልፎ ላም አግብቶ ዘመኑን ሙሉ ሲወጋ ይኖራል:: አንዳንዱም ድመት አግብቶ ዕድሜ ልኩን ሲቧጨርና አንዳንዱ ደሞ ጅግራ አግብቶ ሕይወቱ ሰዶ የማሳደድ ሊሆን ይችላል:: አህያም የሚያገባ እንዲያ ነው። ዕድሜ ልኩን መረገጥ ነው ዕጣ ፈንታው። (ምሳሌያዊ አነጋገር ነው ደሞ ሆሆ. . . ወደ አዳም እንመለስ)
3. የምትረዳ አጥንት
እግዚአብሔር ከአዳም እኩል የፈጠራት ሴት ነገር ግን በወንድ ውስጥ የሰወራት ሴት መገለጫዋ አሁን እንደሆነ የሚወስነበት ሰዓት መጣ:: ስለዚህ እግዚአብሔር አዳም ጥልቅ እንቅልፍ እንዲወስደው አደረገ:: ይሄን ሀሳብ ብዙ የጋብቻ አስተማሪዎች እግዚአብሔርን በጸሎት መጠበቅ ማለት ነው ብለው ሲያስተምሩ እሰማለሁ:: እንቅልፍና ጸሎት ምን አንድ እንደሚያደርጋቸው ግን አላውቅም:: ሊሆን ይችላል::
(እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፥ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው። ዘፍ 2:21)
አዳም በእንቅልፍ ላይ ሳለ በአዳም ውስጥ የደበቃትን ሴት እግዚአብሔር ገለጣት:: መጽሐፉ እግዚአብሔር ከአዳም ጎን የወሰደው አንድ አጥንት ነው ይላል:: የወንድ የግራ ጎኑ ከቀኙጋ እኩል አይደለም ይባላል:: ሳይንስ ያረጋግጠው አያረጋግጠው እንጃ:: ግን እግዚአብሔር ያቺን አጥንት ሴት አርጎ ፈጠራት ይላል:: እዚህጋ የተፈጠረው ማደሪያ ነው። አስቀድማ ከአዳምጋ ለተፈጠረችው ሴት (እኔ መንፈስ ነው የምለው) መገለጫ:: አዳምምኮ ሴት አልታይ ያለችው መንፈስ ብቻ ስለሆነችበት ነው። የምትገለጥበት የስጋ ቤት ካልተሠራላት ፍፁም ሊያገኛት አይችልም ነበር። ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር በኪነ ጥበቡ ያቺን ታናሽ አጥንት ሴት አድርጎ ወደ አዳም ይዟት ይመጣል:: አቤት እንዴት ድንቅ ነው!
(እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት። አዳምም አለ፦ ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል። ዘፍ 2:22-23)
አዳምም ወዲያውኑ እንዳየ ያውቃታል:: በኔ ትርጉም ይወዳታል:: ያፈቅራታል:: ምክንያቱም በርግጥም እርሱን የምትመስለው ረዳቱ ይህቺ ናትና:: መልካም ትዳር ያላቸው ሰዎች ሲናገሩ የትዳር አጋራቸውን ሲያገኙ ወንዶቹም ሴቶቹም አጋሮቻቸውን የሚያውቁዋቸው ያህል የሚሆነው ለዚህ ይሆን እንዴ? ብዬ አስባለሁ::
ሚስት የምትገለጥ እንጂ የምትፈጠር አይደለችም:: ትክክለኛዋ ረዳታችን ከጎናችን ናት:: ከጎናችን እንድትወጣ ግን እንቅልፍ መተኛት አለብን:: እንቅልፍ ሲተረጎም ምንድን ነው? . . . እንደኔ ተዘጋጅቶ መገኘት ይመስለኛል:: . . . የምትገለጠውን ሴት ለማስተናገድ ለአቅመ አዳም መድረስ ከባዱ እንቅልፍ ነው:: አቅም ከምን ከምን አንጻር? . . . ከብዙ ነገር አንጻር:: ዋነኛው ግን ከዕድሜና አካል መደርጀት አንጻርና ከስነ ልቡና ብቃት አንጻር ነው:: ሌላው ተጨማሪ ነው::
ተፈጠመ።
ራስ ዳ. እንደጣፈው
ጁላይ 6/2017
ሲልቨር ስፕሪንግ፣ ሀገረ ማርያም
This entry was posted in AK 3:16, የክርስቲያን ማስታወሻ- Christian Diary, Backlog - ማህደረ ጉዞ, Church - ቤተክርስቲያን, Essay-ወግ, Family - ቤተሰብ, Gospel - ወንጌል, Identity - ስብዕና, Marriage - ትዳር. Bookmark the permalink.

Leave a comment